ይህንን “የእግዚአብሔር ልጅ” የተሰኘ ድንቅ መጽሐፍ ከጥግ እስከ ጥግ ያነበብኩት በብዙ ፍላጎትና በተማሪ ልብ ነው። ነገረ ክርስቶስን የመሰለ ከባድ አስተምህሮ በሚያስገርም ጥልቀት፤ ግን ብዙኀን ሊረዱት በሚችሉት ግልጥነትና ፍሰት መጻፍ አስደናቂ ሊቅነት ነው። ወንድማችን ጳውሎስ ፈቃዱ እንዲህ ዐይነት ተሰጥኦ በጸጋ የተቸረው ሰው ነው። መጽሐፉ በዋንኛነት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ላይ ያተኰረ ቢሆንም፣ የትምህርተ ሥላሴን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ይተነትናል። ወቅታዊ አከራካሪ ጕዳዮችንም በማንሣት ግልጽ ምላሾችን ይሰጣል። በእኔ አመለካከት ይህ መጽሐፍ የእምነታችን ማዕከል የሆነውን ክርስቶስን በተሻለ ጥልቀት እንድንረዳ የሚያግዝ ስንቅ፣ እምነታችንንም ከስሕተት እንድንመክት የሚረዳ ትጥቅ ነው።መጽሐፉን አንብቤ ስጨርስ፣ “ለካ! ጥልቅ የሆነ የምርምር መጽሐፍ ሣር ሣር እንዳይል ተደርጎ ሊጻፍ ይችላል” እንድል ሆኛለሁ፤ ስለዚህ ስጦታው እግዚአብሔርን አመስግኛለሁ። ዮሐንስ መሐመድ (መጋቢ)